60 ሺሕ ቻይናዊያንን ያፈናቀለው ከባድ ጎርፍ

ከሰሞኑ በተለያዩ ሀገራት የሚከሰቱ ኃይለኛ የጎርፍ አደጋዎች ሕይወት የሚቀጥፉ፣ ሃብትና ንብረት የሚያወድሙ በአጠቃላይ ከባድ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሆነዋል። አውራ ጎዳናዎችና መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ ተጥለቀለቁ የሚሉ ዜናዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው። ይህን መሰል የጎርፍ አደጋ ዛሬ በቻይና ተከስቶ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።

በቻይና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት በሚስተዋልበት የጓንግዶንግ የባህር ዳርቻ ግዛት ለቀናት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው ጎርፍ ወደ 60 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተሰምቷል። 11 ሰዎች የጠፉ ሲሆን እስካሁን በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

በመንግስት ሚዲያዎች እና በበይነ መረብ ላይ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጎርፍ የተጥለቀለቀ ሰፊ መሬት ላይ የነፍስ አድን ሰራተኞች በጀልባዎች በጥልቅ እና ሰፊ ውሃ ላይ ሲንሳፈፉ ያሳያሉ።

ትላልቅ ወንዞች ሞልተው በዳርቻቸው ጎረፍ ይፈሳል። የሀገሪቱ የሚቲዎሮሎጂ ባለስልጣናት አደገኛውን ሁኔታ እና ከፍተኛውን የውሃ መጠን በቅርበት እየተከታተሉ መፍትሄ የሚሉትን ሁሉንም እየሞከሩ ናቸው ተብሏል።

በሰሜናዊ ጓንግዶንግ ግዛት የሚገኘው ትልቅ ወንዝ በቻይና መደበኛ ሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ማለዳ ላይ በ100 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ሊሞላ እንደሚችል የሚቲዎሮሎጂ ባለሞያዎች አስጠንቅቀው ነበር። ምንም እንኳን ይህ እስከ እኩለ ቀን ድረስ እውን ባይሆንም።

127 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖሩበት የሚነገረው አብዛኛው የጓንግዶንግ የባህር ዳርቻ አካባቢ የዚህ ትልቅ ወንዝ የተፋሰስ አካል በመሆኑ የወንዙ ውሃ መጨመር ለጎርፍ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል።

የግዛቱ ዋና ከተማ ጓንግዙ እንዲሁም ትናንሽ ከተሞች ሻኦጓን እና ሄዩዋን የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ከመላው የግዛቱ አውራጃዎች ቅዳሜና እሁድ ወደ 1 ነጥብ 16 ሚሊዮን የሚጠጉ አባወራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸው የነበረ ሲሆን ነገር ግን ከዚህ መጠን 80 በመቶ ለሚሆኑት እሁድ ምሽት ተመልሶላቸዋል።

በዋና ከተማዋ ጓንግዙ ውስጥ የሚገኘው ባዩን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተከታታይ ቀናት በጣለው ዝናብ ምክንያት በረራዎች ተሰርዘዋል። ትምህርት ቤቶች ቢያንስ በሶስት ከተሞች እንዲዘጉ ተደርጓል።

በግዛቱ ውስጥ በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ወደ 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰም ይገመታል። በበይነ መረብ በሚሰራጩ ቪዲዮዎች በፍጥነት የሚንቀሳቀሱ ጅረቶች እና የሚፈራርሱ ግድግዳዎች ይታያሉ።

አንዲት የዌይቦ ማኅበራዊ መድረክ ተጠቃሚ “ኃይለኛው ዝናብ የቤታችንን የመጀመሪያ ፎቅ ግማሹን አጥለቅልቆታል” ስትል እሁድ ምሽት ጽፋለች። የቻይና የሚቲዎሮሎጂ ባለሞያዎች በጓንግዶንግ እና በፉጂያን አጎራባች የባህር ዳርቻ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ እስከ ማክሰኞ ድረስ እንደሚቀጥል አስጠንቅቀዋል።