1600 ዓመታትን ያስቆጠሩ ቅርሶች የሚገኙበት የግል ሙዚየም

በሐረር ከተማ የሚገኘው የቀድሞው የተፈሪ መኮንን ታሪካዊ ጫጉላ ቤት አሁን ታሪካዊ ቅርሶች ተሰባስበው የተቀመጡበት የኢትዮጵያውያን፣ የውጭ አገር ዜጎችንና ቱሪስቶችን ቀልብም የሚስብ ልዩ ሙዚየም ሆኗል።

ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የተለያዩ እምነቶች እንዲሁም ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ በ10ሺዎች የሚገመቱ ቅርሶችን አሰባስቦ የያዘ ነው፤ በበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚው በሀረሚያ ዩኒቨርሲቲ የክቡር ዶክትሬት በተበረከተላቸው ውልደት፣ እድገት፣ ትዳር እና ኑሯቸውም በሀረር ከተማ የሆነው አብደላ አሊ ሸሪፍ የመሰረቱት “ሸሪፍ ሙዚየም”።

ከ1600 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ቅርሶች፣ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ መገልገያ የነበሩ ሳንቲሞች፣ የትየለሌ ዓመታትን ህልው መሆን የቻሉ የሃይማኖት መጻሕፍት፣ የነገስታት ሰይፍ እና መሰል የጦር መሳሪያዎች፣ ንጉሳዊያን የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ የተፈረሙ ውሎች እና ሌሎችም እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ታሪካዊ ቅርሶችና ሰነዶች በሸሪፍ ሙዚየም ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ተቀምጠዋል።

በቀደምት ሀረሬዎች የተዘጋጁ በአረብኛ ፊደል በኦሮሚኛ ቋንቋ የተጻፉ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት፣ በሀረር እናቶች በጥበብ እና በጥንቃቄ የተሳሉ የሃይማኖት መጻሕፍት ሽፋን እንዲሁም ሌሎች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ መጻሕፍት በሙዚየሙ ውስጥ እንደልብ ማግኘት ይቻላል፡፡

ሀረሬዎች ይገለገሉባቸው የነበሩ ሳንቲሞች እኛ በዚህ ዘመን ከምናውቃት አምስት ሳንቲም በመጠን 3 እጥፍ የሚያንሱ ሲሆን በአስገራሚ መልኩ በዚች እጅግ ጠባብ ዲያሜትር ባላት ሳንቲም ውስጥ “ነብዩ መሀመድ የአላህ መልዕክተኛ” የሚል ጽሑፍ ታትሞ ይታያል።

ከ1600 ዓመታት በፊት መገበያያ የነበሩትን የአክሱም ሳንቲሞችን ጨምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሉ ገንዘቦች እና በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎችም ግብይት ይፈጸምባቸው የነበሩ ጥንታዊ ገንዘቦች በሙዚየሙ ውስጥ ከአስፈላጊው ገለጻ ጋር በክብር ተቀምጠው ትውልድ ይጎበኛቸዋል፣ ይደነቅባቸዋል፣ ታሪክ ይማርባቸዋል።

የሀረሪዎች ባህላዊ አልባሳት፣ ሀረሪዎች እና ሌሎች ብሄረሰቦችንም ቀደምት ታሪክ የሚያንጸባርቁ ቅርሶች እና በብራና ላይ የተጻፉ ሰነዶችም በአብደላ ዓሊ ሸሪፍ በተመሰረቱ “ሸሪፍ ሙዚየም” ይገኛሉ።

ሐጂ አብደላ ዓሊ ሸሪፍ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቅርስ የማሰባሰብ ስራቸውን የጀመሩት ገና በልጅነታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የሚሰበስቧቸው ቅርሶች በአይነትም በመጠንም እየጨመሩ፤ የጎብኚዎችም ቁጥር እያደገ መጥቶ ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቶ በ1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ምናልባትም በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የግል ሙዚየም “ሸሪፍ ሙዚየም’’ ለመመስረት በቃ።

ይህ ሙዚየማቸው ከሀገር አልፎ የበርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎችንም ጭምር ትኩረት የሚስብ መሆኑን ተከትሎ በ1999 ዓ.ም የሐረሪ ክልል መንግስት ለቅርስ ጥበቃ በሰጠው ትኩረት እና ሐጂ አብደላ ሸሪፍ እያከናወኑት ላለው የቅርስ ማሰባሰብና ጥበቃ ተግባር ውጤታማነት ቀድሞ የተፈሪ መኮንን ጫጉላ ቤት የነበረውና ታሪካዊ ቤት ለዚሁ የቅርስና ታሪክ ጥበቃ ተግባር እንዲውል በመወሰንና በዚያ ለነበሩ ነዋሪዎችም ተለዋጭ ቤት በመስጠት ሙሉ ህንፃውን ለሙዚየምነት እንዲገለገሉበት ሰጥቷቸዋል።

በግል ሙዚየሙ ውስጥ ቅርሶችን ከመሰብሰብ ባለፈ ቅርሶችን የመመዝገብና የመንከባከብ እንዲሁም የተጎዱ ቅርሶች የመጠገንና የማደስ ስራዎችም ይከወናሉ። ለዚህ ተግባራቸው ሐጂ አብደላ ዓሊ ሸሪፍ ከተለያዩ ተቋማት የተለያዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

                                                                                                የሸሪፍ ሙዚየም መስራች ሐጂ አብደላ ዓሊ ሸሪፍ

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ “የሀገራችንን ጥንታዊና ዘመናዊ ስልጣኔዎችን በዓለም ህዝቦች እንዲታወቁ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል” በማለት በ2013 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም የሹዋሊድ ክብረ በዓል በሐረር ከተማ መከበር ሲጀምር በተዘጋጀው የጁገል ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይም አብደላ ዓሊ ሸሪፍ በግል ተነሳሽነት ሙዚየም ያቋቋሙና ልዩ ልዩ ቅርሶችን ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰብሰብና በማስጎብኘት ሥራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከሦስት አስርታት በላይ በቅርስ ጥበቃና ክብካቤ በመሰማራትና የግል ሙዚየም በማቋቋም በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ሐጂ አብደላ ዓሊ ሸሪፍ አሁን አራት የኢግዚቢሽን ክፍል፣ ሁለት መጋዘን፣ አንድ ቡክ ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም አንድ ቡክ ባይንዲንግ እንዳላቸው ነግረውናል።

 

በብርሃኑ አበራ